News Titles News Titles

«Back

ሚያዝያ 8 ቀን 2008

የሁለተኛዉ ዕትዕ በተሻለ መልኩ የሴቶችንና ህፃናትን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዕቅድ መሆኑ ተገለጸ


የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የተለያዩ መስሪያ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የሴቶችንና የህፃናት ጉዳዮች በሴክተሮች ዕቅድ በአግባቡ መካተቱን የሚገመገም የከፍተኛ አመራሮች የፓናል ዉይይት ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በዉይይቱ ወቅት የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ እንዳሉት መድረኩ በዋናነት የተዘጋጀዉ የስርዓተ ፆታ ጉዳይ በሁሉም የሴክተር መ/ቤቶች በአግባቡ መካተቱንና አለመካተቱን ለመገምገም እንዲሁም አፈፃፀሙንም ለመፈተሽ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መድረኩ በተጨማሪም የሴቶችና የህፃናት ጉዳዮች በዝርዝርና በጥልቀት ከማካተት አኳያ በጋራ ታይቶ ክፍተት በታየባቸዉ ላይ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማሳየት እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሲያደርጉ

ኮሚሽነሩ አክለዉም በሁለተኛዉ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሰፊዉ ትኩረት የተሰጠዉ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ሴክተሮች በዕቅዳቸዉ በአግባቡ እንዲያካትቱና ሀላፊነትም ጭምር እንዳለባቸዉ፣ እንዲሁም አመራሩ ትኩረት በመስጠትና በባለቤትነት መንፈስ በተገቢ ሁኔታ ማስፈፀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ፈጣን፣ መሰረተ ሰፊና ቀጣይነት ያለዉ ዕድገት ለማስመዝገብ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባና በየሴክተሩ ምን ያህል ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ናቸዉ፡፡ ሚኒስትሯ በሁለተኛዉ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተቀመጡት መሰረታዊ አቅጣጫዎች አንዱ የሴቶችንና የወጣቶችን ብቃት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ በመሆኑ የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ይህንን ሀይል ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አክለዉ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በዕለቱ ሶስት ዕሁፎች ቀርበዉ የፓናል ዉይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ የመጀመሪያዉ ጽሁፍ ያተኩረዉ በ 13 ሴክተሮች በሁለተኛዉ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሴቶችን ተጠቃሚነትና እንዲሁም የህፃናትን መብትና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የታዩ ጠንካራ ጎኖችና ዉስንነቶችን የሚዳስስ ግብረ መልስ ሲሆን የሁለተኛዉ ጽሁፍ ትኩረት ደግሞ የ 8 የዕድገት ተኮር መስሪያ ቤቶች የሥርዓተ ፆታ ከማካተትና ተቋማዊ ከማድረግ አንፃር የዕቅድ አፈጻጸማቸዉን የገመገመና ዓላማዉም ሴክተር መ/ቤቶች ሴቶችን በማብቃትና ስርዓተ ፆታ ማካተትን ተቋማዊ በማድረግ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናዉኑትን ተግባራት እና የሚመዘገቡት ዉጤቶችን በመመዘንና ተከታታይ ድጋፍ በመስጠት በሁሉም ዘርፍ የሴቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የሀገራችንን የልማት ራዕይ ለማሳካት፣ እንዲሁም ሴክተሮቹ ላስመዘገቡት ዉጤት ዕዉቅና ለመስጠትና ለማበረታታት እንዲሁም ተሞክሮ ቀምሮ ለማስፋፋት እንዲቻል የሚያመላክት የግምገማ ሪፖረት ነዉ፡፡
በመጨረሻም የሴቶች ዉሳኔ ሰጭነትና አመራር ሚና ላይ ያተኮረ የሀገራዊ ጥናት የተጠቃለለ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሴቶች በአመራርነትና ዉሳኔ ሰጭነት ያላቸዉን ተሳተፎ በመለየትና እና ስትራቴጂ በመንደፍ በሁሉም ደረጃ ባሉ የአመራርነትና ዉሳኔ ሰጭነት ቦታዎች የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (ዕትዕ) ላይ የተጣለዉን ሀገራዊ ግብ ማሳካት የጥናቱ አላማ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በማጠቃለያም በቀረቡ ጽሁፎች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በብሔራዊ የፕላን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ እና በሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ በኩል ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የዉይይት መድረኩም በብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን፣ በሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴርና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ ነዉ፡፡